የሀገራችንን የቆዳ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ሀገራዊ ኢኮኖሚውና የስራ ዕድል ፈጠራ ለማሻሻል ሞጆን የቆዳ ፋብሪካ ከተማ(የቆዳ ኢንዱስትሪ መንደር) ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ህብረተሰብ በሚጠቅምና አገራችን ከምትከተለው አረንጓዴ ኢንዱስትሪ ልማት ጋር በተጣጠመ መልኩ በኢንዱስትሪ መንደሩ ተረፈ ምርት አካባቢያዊ ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጋራ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ ለመገንባትና በዘርፉ አገሪቱ ከአፍሪካ ያላትን ድርሻ ወደ መሪነት መቀየር የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተሰራ በመሆኑ ለዘርፉ (የቆዳ ፋብሪካ) ባለቤቶች ስለፕሮጀክቱ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በሂልተን ሆቴል የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአግሮ ፕሮሰሲንግና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገ/እየሱስ የቆዳ ዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አበርክቶና የስራ ዕድል ፈጠራ ለመጠቀም የቆዳ ኢንዱስትሪ ክላስተር (መንደር) መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ ከ8 ዓመታት በፊት የተጀመረውን ሞጆን የቆዳ ፋብሪካ መንደር በማድረግ የዘርፉን እምቅ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የገንዘብና በዩኒዶ (UNIDO) ቴክኒካል ድጋፍ በአካባቢው ያሉትን አርሶ አደሮች የወደፊት የኑሮ ደረጃ በሚያሻሽል መልኩ ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ካሳ በመክፈል አካባቢውን ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ተወካይ አቶ ወንዱ ለገሰ አጠቃላይ ሀገራዊ የቆዳ ዘርፉን አሁናዊ ዳራ ከአለማቀፉ የዘርፉ እንቅስቃሴና ዕድገት በማነፃፀር ለፕሮጀክቱ ስኬት ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦች መነሻ ሰነድ በማቅረብ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡
Source: http://www.motin.gov.et/