15.5 C
Addis Ababa
October 4, 2023
Local News

የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ድርሻ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ባለሙያዎች ገለጹ

ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው የጃፓንና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ከፍተኛ የምክክር መድረክ ወቅት በቀረቡ የጥናት ውጤቶች መሠረት፣ የአገሪቱ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚጠበቀውን ውጤት ከማስገኘት ይልቅ እያሽቆለቆለ እንደመጣ ታይቷል፡፡
በጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) እና በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ትብብር በተሰናዳውና፣ ማክሰኞ ጥቅምት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደው ከፍተኛ የፖሊሲ ምክክር መድረክ ወቅት የልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪው ፀጋዬ ገብረ ኪዳን (ዶ/ር) እና የሙያ አጋሮቻቸው ባቀረቡት ጥናት መሠረት፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪው በተለይም በመካከለኛና በትልልቅ አምራቾች ዘንድ የታየው ማሽቆልቆል ከፍ እያለ መጥቷል፡፡

እንደ ምሁራኑ ጥናት ከሆነ፣ ከ15 ዓመታት በፊት ዘርፉ የፈጠረው 29 በመቶ የሥራ ዕድል ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገ ዳሰሳ ወደ 11 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ በዚሁ ጊዜ ውስጥ ዘርፉ ያደረገው የእሴት ጭመራም ከሰባት በመቶ ወደ አራት በመቶ ዝቅ ማለቱን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡

ዓምና በ137 ከጨርቃ ጨርቅና አልበሳት አምራቾች በተሰበሰበ የመጀመርያ ደረጃ መረጃ መሠረት፣ ዋና ዋና ችግሮች ተብለው በፋብሪካዎቹ የተጠቀሱ የምርታማነት ችግሮች ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትበቂ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት አለማግኘትየሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖርየፋይናንስ አቅርቦትየውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር፣ እንዲሁም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ችግሮች ጎልተው ይጠቀሳሉ፡፡

በምሁራኑ ጥናት መሠረት በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እየተቸገሩ ከሚገኙት ፋብሪካዎች ውስጥ 42 በመቶዎቹ ዋና ችግራቸው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በአንፃሩ የኢትዮጵያን መንግሥት በኢንዱስትሪ ፖሊሲ ረገድ ለረዥም ዓመታት እያማከሩ የሚገኙት ጃፓናዊው ፕሮፌሰር ኪኒቺ ኦህኖ፣ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ከሴሪላንካ ጋር በማነጻጸር ባቀረቡት ጽሑፍ ውስጥ በኢትዮጵያ ያለው ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የውጭ ኩባንያዎችን ከሚስቡ ማበረታቻዎች ውስጥ እንደሚጠቀስ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በኪሎ ዋት ኃወር ለኤሌክትሪክ ፍጆታ የሚከፈለው አራት የአሜሪካ ሳንቲም (በአሁኑ ምንዛሪ 10.8 ብር) እንደሆነ ጠቅሰው ይህ በስሪላንካ ከ16 ሳንቲም ወይም ከ43 ብር በላይ በመሆኑ ኢትዮጵያን ተመራጭ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ከሚያደርጓት መካከል እንደሚመደብ ፕሮፌሰሩ ጠቅሰዋል፡፡
ምንም እንኳ ለሠራተኞች የሚከፈለው ደመወዝ ስሪላንካን ጨምሮ ከሌሎችም የእስያ አገሮች አኳያ ዝቅተኛ እንደሆነና በቀላሉ ለፋብሪካ ሥራዎች ሊሠለጥን የሚችል የሰው ኃይል መኖሩ ቢጠቀስም፣ የአገር ውስጥ አምራቾች ተወዳዳሪ መሆን እንዳልቻሉ፣ ይልቁንም በውጭ ተወዳዳሪዎቻቸው እንደተዋጡ ፕሮፌሰር ኦህኖ አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ምሁራን ከቀረቡ ምክረ ሐሳቦች መካከል መንግሥት የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ፖሊሲዎችን እንዲፈትሽ ከመጠየቅ ባሻገር፣ ሠራተኞችን በሥራ ላይ ለማቆየት ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች እንዲሰጡ፣ መንግሥትም ኩባንያዎች ለሠራተኞቻቸው በሚሰጡት ማበረታቻ ላይ ድጎማ እንዲያደርግ ከሚጠይቁት ውስጥ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡

በአገሪቱ የተገነቡት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ የማድረግ አቅማቸው ትልቅ እንደሆነ የገለጹት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ ፍፁም አረጋ፣ በተለይ ከቦሌ ለሚና ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች እየለቀቁ መሄዳቸውን አስታውቀዋል፡፡ በተለይ በቦሌ ለሚ ከተቀጠሩት ውስጥ 40 በመቶዎቹ በወራት ጊዜ ውስጥ ለቀው ወጥተዋል ያሉት አቶ ፍፁም፣ አብዛኞቹም በሚከፈላቸው ዝቅተኛ የወር ደመወዝ መነሻነት እንደሚለቁ፣ የሚቀጥሯቸው ፋብሪካዎችም ተገቢውን ማበረታቻ እንደማይሰጣቸው ጠቅሰው፣ ለሠራተኞች ተገቢውን ጥቅማ ጥቅምና ማበረታቻ መስጠት የቻሉ ኩባንያዎች ሠራተኞቻቸውን ማቆየት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ከአሥር ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የአገሪቱ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ በዓመት የ30 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘት እንደሚጀምር ሲናገር ይደመጣል፡፡ ይኼውም የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ዞንን ጨምሮ በአገሪቱ እየተገነቡ ያሉት ሌሎችም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚያስገኙት ውጤት ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ እየተገኘ ያለው ገቢ ከ150 ሚሊዮን ዶላር በታች ሆኖ ይገኛል፡፡

Source: https://www.ethiopianreporter.com/

Related posts

An Updated Approach to Addressing Foreign Exchange Supply Challenges in the Manufacturing Industry

Areda Batu

Bahir Dar University Opened an Exhibition for the University Community on June 5, 2023, Showing 60 years of Journey.

Areda Batu

Ethiopian Textile and Apparel Professional Association Founded

Areda Batu

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy
Show Buttons
Hide Buttons