የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ወተር ዊትነስ ኢንተርናሽናል ከተባለ የልማት ድርጅት ጋር በሃገራችን ለሚገኙ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ የሚውል 21 ሚሊዮን 72 ሽህ 26 ብር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡በስምምነቱ ላይ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የቆዳና ጨርቃጨርቅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን አበበ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ለሚገኙ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ ለማድረግ ያሳየው ተነሳሽነት የሚደገፍ መሆኑን ጠቁመው ኢንዱስትሪዎቻችን በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ያሉባቸውን ክፍተት ለመድፈን ከፕሮጀክቱ ጋር የተደረገውን ስምምነት ስኬታማ ለማድረግ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የማስተባበር ስራ ይሰራልም ብለዋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ የአግሮ-ፕርሰሲንግና ፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አማካሪ አቶ ጳውሎስ በርጋ በበኩላቸው ሃገራችን ለምትከተለው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ የውሃ ሃብታችንን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸው ለዚሁም ስኬት የዛሬው ስምምነት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወጣም ገልጸዋል፡፡
ወተር ዊትነስ ኢንተርናሽናል የተባለውን ድርጅት ወክለው ስምምነቱን የፈረሙት የአፍሪካ ፕሮግራም ማናጀር አቶ ኢሳያስ ሳሙኤል የፕሮጀክቱ ተቀዳሚ ዓላማ በሃገሪቱ የሚገኙ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍን በተለይም በውሃ አጠቃቀማቸው ዙሪያ ያላቸውን ክፍተት ለመሙላት መሆኑን ገልጸው ለዚህም ዓላማ 500, 000 ፓውንድ ተመድቧል ያሉ ሲሆን ይህንን ዓላማ ለማሳካት ድርጅቱ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ በተጓዳኝ ከሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አስረድተዋል፡፡
Source: http://www.motin.gov.et/