ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኢትዮጵያ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት ማቀድዋንሲ ጂቲ ኤን አፍሪካ ያወጣው ዘገባ ያመለክታል።
አሁን ስራ ከጀመሩ 5 ኢንዲስትሪ ፓርኮች በተጨማሪ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 የፓርኮቹን ቁጥር 30 ለማድረስ እየሰራች እንደሆነም ተጠቅሷል።፡
ኢትዮጵያ ትልቅ ራዕይ በመሰነቅ በአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለመሆን የኢንዲስትሪ ፓርኮችን በቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ ላይ ትገኛለችም ብሏል ዘገባው፡፡
በስራ ላይ የሚገኘው የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለ23 ሺ ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩን እና ለበርካቶች የስልጠና ማእከል ሆኖ እያገለገለ እንደሆነም ሲጂቲኤን አፍሪካ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ አቶ መኮንን ሃይሉን ዋቢ አድርጎ ዘግቧዋል፡፡
ዥንዋ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሌሊሴ ነሜን ጠቅሶ እንደዘገበው እስካሁን ድረስ አምስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብቶ ስራ መጀመራቸውን እና በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2018/19 ተጨማሪ 6 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡
ቅሊንጦ፣ ድሬዳዋ፣ ቦሌ ለሚ 2፣ ባሃርዳር፣ አረርቲ እና ደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተያዘው 2018/19 የበጀት ዓመት ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃልም ብለዋል ሃላፊዋ፡፡
ደብረ ብርሃን እና አረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በቻይና ኮሙኒኬሽንስ ኮንስትራክሽን ኩባንያ(CCCC) እየተገነቡ ሲሆን የድሬዳዋ እና የባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርኮች በቻይና ሲቪል ኢንጅነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን አማካኝነት እየተገነቡ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቁጥር ወደ 30 በማሳደግ የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ማእከል በመሆን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ እየሰራች ነው ሲል ነው ሲጂቲኤን አፍሪካ የዘገበው፡፡
Source: http://www.obn.et/