በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ጥሬ እቃ ስም በስምንት ኮንቴነር የታሸገ ያለቀለት የኤሌክትሮኒክስ እቃና አልባሳት ወደ ሃገር ውስጥ ሊገባ ሲል መያዙን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታወቀ።
በባለስልጣኑ የሞጆ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የጉምሩክ ስነ-ስርዓት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ግርማ በንቲ እንደገለጹት እቃው የተያዘው ተመሳስሎ ሊያልፍ ሲል በሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ ነው።
በአምስቱ ኮንቴነሮች የተያዘው ለጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የሚውል ብትን ጨርቅ እንደሆነ ተመስክሮለት በጁቡቲ ወደብ የገባ ቢሆንም በተደረገ ፍተሻ ከምርት ጋር ተመሳስሎ የታሸገ 410 ቦንዳ ያለቀለት አዳዲስ አልባሳት ሆኖ ተገኝቷል።
ከተያዙት አልባሳት መካከልም ያለቀለትና ለገበያ ሊበተን የሚችል በርካታ ዘመናዊ ጃኬትና ሱሪ እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።
በሶስቱ ኮንቴነሮች የተያዘው ደግሞ ለፋብሪካ በጥሬ እቃነት የሚውል የክር ማግ መሆኑን ተመስክሮለት ወደ ሀገር ውሰጥ እንዳይገባ የተከለከለ የኤሌክትሮኒክስ እቃ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኤሌክትሮኒከስ እቃው በ1 ሺህ 500 ካርቶን የታሽገ በለ 200 ዋት 75 ሺህ አምፖል መሆኑንም አመልክተዋል።
“ይህ ምርት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አባካኝ መሆኑ በሚመለከተው የመንግስት አካል የተረጋገጠ በመሆኑ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ የተከለከለ ነው” ብለዋል።
የንብረቱ የዋጋ ግምት እየተሰላ መሆኑን ገልጸው ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ ጉዳዩ እንዲጣራ ለጉምሩክ ህግ ማስከበርና ምርመራ ክፍል መተላለፉን አስታውቀዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ